ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 11 ጊዜ ድል ሲቀናው ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 39 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 33 ጎሎችን አስተናግዷል።
በ47 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ አርን ስሎት የሚመራው ሊቨርፑል በ39 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ማንችስተር ሲቲ በሊጉ እስከ አሁን ባካሄዳቸው 24 ጨዋታዎች 14 አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ በተመሳሳይ አመስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 49 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 23 ግሎች ተቆጥረውበታል።
በ55 ዓመቱ ስፔናዊ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንችስተር ሲቲ በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 199 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሊቨርፑል 95 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ማንችስተር ሲቲ 51 ጊዜ ሲያሸንፍ 53 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ 57 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል 23 ጊዜ ሲያሸንፍ ማንችስተር ሲቲ 13 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 21 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
በ24ኛ ሳምንት ኒውካስትል ዩናይትድን 4 ለ 1 በማሸነፍ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ሊቨርፑል የዛሬው ጨዋታ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ ለሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ነው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወጥነት የሌለው ብቃት እያሳየ ይገኛል።
በሊጉ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር ሁለት አቻ የወጣው ማንችስተር ሲቲ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የዛሬው ድል ያስፈልገዋል።
ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ የሊጉ መሪ አርሰናል ጋር የሚኖረው የግብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ ይላል።
የ46 ዓመቱ ክሬግ ፖውሰን ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ብራይተን ከክሪስታል ፓላስ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በአሜክስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።