ቀጥታ፡

ማህበሩ ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን ይወጣል

አምቦ፤ጥር 30/2018(ኢዜአ)፡- የምዕራብ ሸዋ ዞን ወጣቶች ማህበር ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገለጸ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ካሉ ወረዳዎች ለተወጣጡ ወጣቶች በመጪው ጠቅላላ ምርጫና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል።

በወቅቱም የምዕራብ ሸዋ ዞን ወጣቶች ማህበር ኃላፊ ወጣት ሂርጳሳ ገላል እንደገለፀው፤ ማህበሩ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶች ተሳትፎ ከመምረጥና ከመመረጥ ባለፈ ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራ ነው።


 

ማህበሩ የሲቪክ ማህበር እንደመሆኑ መጠን ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ሠላማዊና ተዓማኒነትን ያተረፈ እንዲሆንም የድርሻውን ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብሏል።

ወጣቱ በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን መብት በመጠቀምም በመምረጥ፣ በመመረጥ፣ በማስመረጥና የምርጫውን ሰላማዊነት በማስጠበቅ ረገድ የላቀ ድርሻና ኃላፊነት እንዳለበትም አስገንዝቧል።

ማህበሩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ  እውቅና ያገኘ መሆኑን ገልፆ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም  የተለያዩ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገረው።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ምስጋና ከበደ በበኩላቸው፤ ወጣቱ መጪው ጠቅላላ ምርጫ ከጅምሩ እስከ ማጠናቀቂያው  ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከስልጠና ተሳታፊዎቹ መካከል ከወልመራ ወረዳ የመጣችው ወጣት ትእግስት ኦሊ በበኩሏ፤ ስልጠናው በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ የጠራ ግንዛቤ እንድትይዝ ማድረጉን ገልፃለች።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለውን የተረጋጋ ሰላም በማስቀጠል ምርጫው በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ነው ያለችው።

በመጪው ግንቦት ወር ላይ የሚካሔደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቴክኖሎጂ መደገፉ ወጣቱ ያለምንም ተግዳሮት ተሳታፊ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ያለው ደግሞ ከኢልፈታ ወረዳ የመጣው የስልጠናው ተሳታፊ ወጣት ቦኒ  ወርቅነህ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም