በከተማዋ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ቢሮው
ሆሳዕና ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የሚካሄደውን 6ተኛውን ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ለማስተናገድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለፀ፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንሱን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ስድስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በመጪዎቹ የካቲት 4 እና 5/2018 ዓ/ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሆሳዕና ከተማ ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል ብለዋል።
በሀገር አቀፉ የሰላም ኮንፈረንስ ላይም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚመጡ በርካታ እንግዶች እንደሚሳተፉ ጠቁመው ሲከናወን የቆየው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በአደባባይ በሚከበረው በዓል ላይም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።
የሰላም ኮንፈረንሱ በሲምፖዚየምና በአደባባይ እንደሚዘከር ያነሱት ኃላፊው በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምንና አብሮነትን ለማጠናከር የሚረዱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች በሲምፖዚየሙ ላይ ተሞክሮ ቀርቦባቸው ውይይት እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡