ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የውጭ አገራት አትሌቶች የሚሳተፉበት የግማሽ ማራቶን ውድድር በሀዋሳ ይካሄዳል

ሀዋሳ ፤ጥር 30/2018 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያና የውጭ አገራት አትሌቶች የሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018” ሁለተኛው ዙር የግማሽ ማራቶን ውድድር በሀዋሳ ይካሄዳል።

በነገው እለት በሀዋሳ ከተማ የሚካሄደውን “ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018” ሁለተኛው ዙር የግማሽ ማራቶን ውድድር በተመለከተ በቱሪዝም ሚኒስቴር የፕሮሞሽን ስራ አስፈጻሚ ተሾመ ተክሉ መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በመግለጫቸውም በነገው ውድድር የኢትዮጵያና የተለያዩ አገራት አትሌቶች እንዲሁም ከሀዋሳና የተለያዩ ከተሞች ከ500 በላይ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል።

በአራት ከተሞች ብቻ ሲካሄድ የቆየው ልወቅሽ ኢትዮጵያ ውድድር ዘንድሮ ሀረርና ደብረብርሀንን በመጨመር ወደ ስድስት ከተሞች ማደጉን ገልጸው በቀጣይም በሌሎች ከተሞች የመጀመር እቅድ ተይዟል ብለዋል።

ከውጪ አገራት የሚመጡ አትሌሎች በውድድሩ መሳተፋቸውም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታና የመስህብ ስፍራዎቿን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው በዚሁ መልኩ በነገው እለት ውድድሩ በሀዋሳ ከተማ ይካሄዳል ብለዋል።


 

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ መቅደስ ሁሪሶ፤ ሀዋሳ የፍቅር ሀይቅን ጨምሮ በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ያሏት በመሆኑ አንስተዋል።

ከተማዋ በተፈጥሮ ከታደለችው መስህብ በተጨማሪ በኮሪደር ልማት ስራ ተጨማሪ ውበት እየተላበሰች ለጎብኚዎች ምቹ መሆኗን ጠቁመው ከዚህ አንፃር የውድድሩ መካሄድ ለከተማዋ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀዋሳ ከተማ ነገ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን የአዋቂዎች እንዲሁም የ8 ኪሎ ሜትር የህፃናት የሩጫ ውደድር በድምሩ ከ650 በላይ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም