ቀጥታ፡

መንግሥት ጠንካራና ዘላቂ የስነ ተዋልዶ ጤና ስርዓት ለመገንባት ከአጋር አካላት ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ጠንካራና ዘላቂ የስነ ተዋልዶ ጤና ስርዓት ለመገንባት ከአጋር አካላት ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።

የኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሃኪሞች ማህበር 34ኛው ዓመታዊና የአፍሪካ የፅንስና ማህፀን ሃኪሞች ፌዴሬሽን 9ኛው ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል። 

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔ "ጠንካራ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ሥርዓት፥ በአፍሪካ የስነ-ተዋልዶ ጤና የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት" በሚል መሪ ሀሳብ  ነው እየተካሄደ የሚገኘው። 

በጉባዔው ከ1 ሺህ በላይ የማህበሩና የፌዴሬሽኑ አባላት እንዲሁም ከ150 በላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት ኢትዮጵያ በስነ-ተዋልዶ ጤና እንዲሁም እናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ተሞክሮ የሚሆን አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። 

የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ የጤና ስርዓት ማዕከል ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑን አንስተው፥ በአፍሪካ ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመዘርጋትም የስነ-ተዋልዶ ጤና ስርዓቱን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

መንግስት ለስነ-ተዋልዶ ጤና ከፖሊሲ ቀረፃ እስከ ትግበራ ድረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥  በዘላቂ የልማት ግቦች የተያዘውን የእናቶችና ህፃናት ሞት የመቀነስ እቅድ ማሳካት መቻሉን አንስተዋል።

በሀገር ውስጥ አምራቾች 40 በመቶ በላይ የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶች እየቀረቡ መሆኑንና የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን የሚመራ ጠንካራ ተቋምና ስርዓት መገንባቱን ተናግረዋል።

በጤና ኤክስቴንሽንና በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አሃድ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና ይህም ለስነ-ተዋልዶ ጤናና ቤተሰብ ምጣኔ መጠናከር አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የእናቶችና ህፃናት ጤና ስርዓትን ጠንካራና ዘላቂ ለማድረግ በአጋርነት መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግስትም በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

የአፍሪካ የፅንስና ማህፀን ሃኪሞች ፌዴሬሽን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሚ መሀመድ በበኩላቸው ጉባዔው የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን የበለጠ ለማጠናከር የሚመከርበት መሆኑን ተናግረዋል።
  

በአባል ሀገራት ላሉ ባለሙያዎች የስራ ላይ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ በምስራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ አፍሪካ የማህፀንና ፅንስ ኮሌጅ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ቫላንቲና ምናሴ ናቸው። 

የኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሃኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ኃይለማርያም ሰኚ እንዳሉት በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። 

በሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶች ምርትን ለማሳፈግ ትኩረት መሰጠቱ፣ የሰው ኃይል ልማትና የህክምና ተደራሽነት ላይ የተሰራው ስራ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነስ ረገድ መንግሥት ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን በማንሳት፥ ማህበሩም ለዚህ ስኬት የበኩሉን ሚና መወጣቱን ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም