የስንዴ ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር የማውጣት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የስንዴ ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር የማውጣት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሰመራ፣ጥር 30/2018 (ኢዜአ)፡- የስንዴ ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር የማውጣት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።
በአፋር ክልል በዱብቲ ወረዳ እየተከናወነ ባለው የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክትና በሰርቶ ማሳያ እየተከናወነ ያለው የስንዴ ዘር ብዜት ስራ የመስክ ምልከታ ዛሬ ተካሄዷል።
በመስክ ጉብኝቱ ላይም በግብርና ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብዱሶመድ አብዱ እንዳሉት በክልሉ የስንዴ ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር የማውጣት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህም በሰርቶ ማሳያ አየተተገበረ ያለውን ምርታማና ተስማሚ የሆነውን የስንዴ ዝርያ ለመለየት መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ በስንዴ ረገድ ምርታማ መሆን እንደሚቻል ያሳየና ምርትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ሊያሳካ የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ አማካሪ ወይዘሮ በላይነሽ ኩምሳ በበኩላቸው በአፋር ክልል ተሰማሚ የሆነ የስንዴ ዝርያን ለማውጣት በሰርቶ ማሳያው አየተከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
ክልሉ ከሚታወቅበት በተጨማሪ ሌሎች እምቅ አቅሞችን ለማውጣት የሚያስችል የስንዴ ምርታማነትን ማሻሻል ላይ ቀድሞ ይሰራበት የነበረውን ዘይቤ በመቀየር በዘርፉ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችልም ተናግረዋል።
በክልሉ በስንዴ ዝርያ ማሻሻል ላይ እየተሰራ ያለው ስራ እንደ አገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እገዛ ይኖረዋል ያሉት የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አህመድ አሚን ናቸው።
በክልሉ ያለውን የመሬትና የውሃ ሃብት በመጠቀምና የግብዓት እጥረቶችን በመቅረፍ በአዋሸ ወንዝ ዳርቻ ላይ በሚገኙ 20 ወረዳዎች ላይ የተጀመረውን ስራ ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በአፋር ክልሎች በሚገኙ 76 ወረዳዎች በመተግበር ላይ መሆኑም ተመላክቷል።