ቀጥታ፡

የመምህራን ማህበራት አቅም መጠናከር በትምህርት ጥራትና በሀገራዊ ዕድገት ላይ የጎላ ሚና አለው

ሀዋሳ ፤ጥር 30/2018 (ኢዜአ):- የመምህራን ማህበራት በኢኮኖሚ አቅም መጠናከር በትምህርት ጥራትና በሀገራዊ ዕድገት ላይ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተመላከተ፡፡

በሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እንዲሁም የሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበራት የጋራ ሕንፃ ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል፡፡

ባለ ስድስት ፎቅ የሆነው ይህ ሕንፃ በቀድሞው የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር አማካይነት በ2008 የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ሥራው የተጀመረ ቢሆንም በመሀል ተጓቶ ቆይቷል፡፡


 

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ የመምህራን ማህበራት በኢኮኖሚ መጠናከር ለትምህርት ጥራትና ለሁለንተናዊ ዕድገት ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡

መምህራን የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት እየተጫወቱት ያለውን አይተኬ ሚና ለማጠናከር እንደሚያግዝም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት  ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ የመምህራን ማህበራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለመምህራን በቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ብሎም የትምህርት ጥራትን የሚደግፉ ሥራዎችን ማከናወን እንዲችሉ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከተመረቀው ሕንፃ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ማህበራት እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች እንዳሉ ጠቁመው በሁሉም ክልሎች መዋቅሮች ባሉ ማህበራት ጅምርና በሂደት ላይ ያሉ ተግባራት አሉ ነው ያሉት።

የመምህራን ማህበራቱ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ጨምሮ በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ መምህራንን በነቂስ እንዲሳተፉ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው በዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ላይም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ሕንፃ ለመምህራን አስፈላጊውን አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በትምህርት ጥራት ላይ የሥልጠና ክፍተቶችን ለመሙላትና የልማት ጥሪዎች ላይ ተሳትፎውን ለማሳደግ የሚጠቅም መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር አማኑኤል ጳውሎስ ሕንፃው በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ለምረቃ መብቃቱን ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ዘግይቶ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር ኢያሱ ፍቅሬ ማህበራት የመምህራንን መብትና ጥቅማ ጥቅም ለማስከበር ከሚሰሩት ሥራ ጎን ለጎን በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይም ለሕንፃው ግንባታ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት የተበረከተ ሲሆን የማህበራት ተወካዮችና አመራር አካላት ተገኝተዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም