ቀጥታ፡

ቀርጫንሼ ግሩፕ እና የብራዚሉ የግብርና ምርምር ተቋም የቡና ቴክኖሎጂ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ጥር 30 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቡና ላኪ ቀርጫንሼ ግሩፕ እና የብራዚሉ የግብርና ምርምር ተቋም በቡና ልማት እና ቴክኖሎጂ ዙሪያ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

የቡና ማምረት ስርዓቶችን በጋራ መቅረጽም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በስምምነቱ መሰረት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ደበቃ ያለውን የቡና ምርት ማሻሻል ስራ ይከናወናል።

የጥራት ደረጃ ስርዓቶችን ማሻሻል እና የግብርና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የስምምነቱ አካል ነው።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

መንግስት የስምምነቱ ትግበራ ውጤታማ እንዲሆን እና የታለመለትን ግብ እንዲመታ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የቀርጫንሼ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ እስራኤል ደገፋ ኢትዮጵያ እና ብራዚል በግብርናው ዘርፍ በርካታ መመሳሰሎች እንዳላቸው አንስተዋል።

የስምምነት ማዕቀፉ የሁለቱን ሀገራት ትብብር የሚያጠናክርና ብራዚል በቡና ልማት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያላትን ልምድ ለማካፈል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።


 

በስምምነት ስነ-ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶ ሳንቶስ እና የብራዚል የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን ፕሬዝዳንት ሲልቪያ ማሪያ ፎንሴካን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮ-ብራዚል የኢኮኖሚ ትብብር ፎረም ትናንት የተካሄደ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና ግብርና ዘርፎች ያላቸውን ስምምነት ማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም