ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማሳደግ የተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማሳደግ የተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ይፋ የተደረገ ሀገራዊ መርሃ-ግብር ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። 

ይህ ንቅናቄ ከመደበኛው የገጠር ግብርና ባለፈ የከተማ ግብርናን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመጠቀም በከተሞች የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ ያለመ ነው።

በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተቀረጸው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በመዲናዋ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው፡፡ 

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ጽጌሬዳ ፍቃድ እንደገለጹት፤ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤት ማምጣት ጀምረዋል። 

የዜጎችን የሥርዓተ-ምግብ ፍላጎት ለማሟላት የተቀረጸው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ለሥጋ፣ ለእንቁላል፣ ለማር እና ለወተት ምርት መጨመር ትልቅ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ መርሃ-ግብር በተለይ የሴቶችና የወጣቶችን ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን ጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታት በዝርያ ማሻሻል አገልግሎት ላይ የታየው ለውጥ እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀንድ ከብቶች ከማዳቀል አንጻር በተከናወኑ ሥራዎችም ቀደም ሲል በዓመት ለ500 ሺህ ከብቶች ብቻ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ስኬት ለማስፋት የተለያዩ ቅርንጫፎች ተቋቁመው በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

በተሻሻሉ ዝርያዎች አጠቃቀም ረገድ የታየው እመርታ ከፍተኛ የምርታማነት ለውጥ ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ ለአብነትም የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶች ስርጭት ከ26 ሚሊዮን ወደ 136 ሚሊዮን ማደጉ የእንቁላልና የሥጋ ምርትን አሳድጓል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የግለሰቦች ዓመታዊ የወተት ፍጆታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው ይህ ውጤት ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ለአንድ ሰው ያስቀመጡትን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት መመዘኛ ለማሳካት ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም