ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በግፍና በሴራ ያጣችው የባህር በር የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ የፍትሐዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው

ሀዋሳ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በግፍና በሴራ ያጣችው የባህር በር የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ የፍትሐዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ “ኢትዮጵያና ተለዋዋጭ ጂኦ ፖለቲካ በአፍሪካ ቀንድ” በሚል ርዕስ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

በውይይቱ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ ዳራ፣ መልክዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ እንዲሁም ምላሽ ሊያገኝ የሚገባ የህልውና ጥያቄ መሆኑን የሚያወሱ ጽሑፎች ቀርበዋል።

የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የዲፕሎማሲ አሰልጣኝና የውጭ ፖሊሲ ተመራማሪ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለዘመናት ከባህር በር ተነጥላ የማታውቅ ብትሆንም በፖለቲካ ሴራ ምክንያት የባህር በሯን እንድታጣ መደረጉን ገልጸዋል።

ይህም የዘመናት የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ የፍትሐዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው የባህር በር ማስመለስ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለባት ነው ያሉት።

የባህር በር ጉዳይ የወደብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ድርሻ እንዲኖራት የሚያደርግ መሆኑ መታወቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሀገራት የባህር ቀረቤታ እንዲኖራቸው በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ ያሉት አምባሳደሩ የኢትዮጵያም አንገብጋቢ አጀንዳ አለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ በዲፕሎማሲው መስክ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ካላት ታሪክ፣ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ዓለም አቀፍ ህግ አንጻር የባህር በር ማጣቷ ተገቢነት እንደሌለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ደመቀ አጭሶ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

ይህ ጥያቄ የሀገሪቱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በዘላቂነት ምላሽ እስኪያገኝ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ትውልዱ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

የባህር በር ጉዳይ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር በመሆኑም ለስኬታማነቱ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት ታፈሰ ማቲዮስ(ዶ/ር) በበኩላቸው አሁን ላይ መላው ዜጋ በባህር በር ጥያቄው ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዲኖረው የማድረግ ስራ መጠናከር አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም