ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በብልፅግና ጎዳና በፍጥነት እየገሰገሰች እንደምትገኝ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ቋሚ ምስክር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በብልፅግና ጎዳና በፍጥነት እየገሰገሰች እንደምትገኝ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ቋሚ ምስክር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።       

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ የተገነባውን የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀዋል።  


   

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የአከባቢውን ጸጋ በገለጠ መልኩ ለውጤት በቅቷል።       

የብልፅግና መንግሥት የማይሰራውን ቃል አይገባም፤ ቃል የገባውንም አይዘነጋም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትም በውጤታማነት መጠናቀቁ ለዚህ አብነት ነው ብለዋል።     

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ኢትዮጵያ በብልፅግና ጎዳና በፍጥነት እየገሰገሰች ለመሆኑ ህያው ምስክር መሆኑንም አመልክተዋል።        

የመደመር መንግሥት ሀገረ መንግሥት ግንባታን የማሳካት ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ጠንካራ፣ የበለፀገች፣ የታፈረች፣ የተከበረች፣ ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን መገንባት በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል መሆኑን አስረድተዋል።   

ለዚህ ደግሞ  የገበታ የልማት ፕሮጀክቶች ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።   


 

የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ሀብት እያፈሩ ሕዝብ እያስተሳሰሩ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የፕሮጀክት አፈጻጸም መመሪያዎች ሆነው እያገለገሉ መሆኑን አብራርተዋል።    

የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችም ተከታታይነት ባለው መልኩ እየተመረቁ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ እያነቃቁ ነው ብለዋል።    


 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የታየው የመሪ ቁርጠኝነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ለቃል መታመን፣ የመፍጠርና መፍጠን መርህን የተከተለ አካሄድ እንዲሁም ጀምሮ የመጨረስ ባህል መዳበሩ በሁሉም መስክ ውጤት እንዲመዘገብ መሰረት መጣሉን ገልፀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም