ቀጥታ፡

በትምህርት ዘርፉ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎችና የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ በትምህርት ሥርዓቱ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገንና ጥራትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ የፖሊሲና የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ከመሠረቱ የማስተካከልና የደረጃ ማሻሻያ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በአጠቃላይ ትምህርት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመሠረተ ልማት ማሻሻያ ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለሚያረጋግጡ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ 

የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች 34ሺህ በላይ የመዋዕለ ሕፃናት መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከአራት ሚሊየን በላይ ሕፃናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ አየለች እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለትምህርት ጥራት መሻሻል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

ለዚህም በነባር የትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ የተመላከቱ ችግሮችን በጥናት በመለየት የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው ለጥራት ቅድሚያ በሚሰጥ መልኩ እንዲሻሻል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት የነበሩበትን ክፍተቶች በዝርዝር በመለየት አዲስና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመው ይህም በዘርፉ ትልቅ ስኬት ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ለማስቻል ብቃትን መሠረት ያደረገ ሆኖ መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት፡፡

ይህም ተማሪዎች የንድፈ ሃሳብ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ክህሎትንም እንዲያዳብሩ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በፖሊሲና በሥርዓተ ትምህርት ደረጃ የተወሰዱት እነዚህ የለውጥ እርምጃዎች በትምህርት ዘርፉ የታየውን ስብራት ለመጠገንና ብቁ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በትምህርት ለትውልድ መርሐ-ግብር ማህበረሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ከመሠረቱ ለማስተካከል ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ንቅናቄ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመው በርካታ ከደረጃ በታች የነበሩ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው እንዲሻሻል መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ 

እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ከአዋኪ ድርጊቶች ነጻ ማድረግ ማስቻሉን ተከትሎ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና በመልካም ሥነ-ምግባር እንዲታነጹ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በዕውቀትና በሥነ-ምግባር የበለጸገ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም