ቀጥታ፡

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ልማት ላይ ያተኮሩ ዓይኖች እና መበልጸግን የሚያሰላስሉ የልቦና ውቅሮች ውጤት ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ልማት ላይ ያተኮሩ ዓይኖች፣ መበልጸግን የሚያሰላስሉ የልቦና ውቅሮች እና በጎ መስራትን የሚያስቡ አዕምሮዎች ውጤት መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በገበታ ለትውልድ ውጥን የተገነባው እና በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀዋል። 


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለአካባቢው ግርማ ሞገስ ያጎናጸፈና ለክልሉ ሁለንተናዊ ልማት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።  

ሪዞርቱ ከሆቴል አገልግሎት ባለፈ ትልቅ የታሪክና የቱሪዝም ድልድይ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ሪዞርቱ አዲስ አበባን፣ ለአድዋ ድል ክተት የታወጀበት ወረኢሉን፣ የውጫሌ ውል የተሰናዳበትን ይስማ ንጉስን፣ ማይጨውንና የጥቁር ህዝቦች የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን አደዋን የሚያስተሳስር የቱሪስት ፍሰት መስመር ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ደሴንና ኮምቦልቻን እንዲሁም በአቅራቢያው የሚገኙ ከተሞችን በማገናኘት ወደፊት ለሚመሰረተው ታላቁ የቀጠናው ከተማ ትልቅ ግብዓት ይሆናልም ብለዋል።


 

አካባቢው በርካታ እድሜ ጠገብ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ መስህቦች ያሉበት ቢሆንም፣ በመዳረሻ ልማት እጥረት ምክንያት ከቱሪስቶች ርቆ መቆየቱን ነው ያስታወሱት፡፡

ዛሬ የተመረቀው ሪዞርት ይህንን ችግር በዘላቂነት በመቅረፍ የሀገርን ገጽታና የህዝብን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ሌሎች መሰል ልማቶችን ለማከናወን አርአያ እንደሚሆንም ገልጸዋል።


 

ሪዞርቱ በጎ መስራትን የሚያስቡ አዕምሮዎች የጋራ ድል መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም