ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለጽዱ ኢትዮጵያና ለአካባቢ ደኅንነት ወሳኝ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያበረከተ ነው - ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለጽዱ ኢትዮጵያና ለአካባቢ ደኅንነት ወሳኝ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያበረከተ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ቅነሳ፣ ለከተማ ውበትና ጽዳት ፋይዳ ያላቸው ምርቶችን በማምረት ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።


 

በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ቅነሳ፣ ለከተማ ውበትና ጽዳት ፋይዳ ያላቸው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን እያበረከተ ይገኛል።  

በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያፋጥኑ ምርቶችን እያመረቱ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ማገዶ ቆጣቢ የሆኑና ለካርበን ልቀት ቅነሳ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ውጤቶች ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረው ይህም በደኖች ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለመታደግ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። 

በከተሞች የሚከናወኑ የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት እና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቶችን የሚያዘምኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልጸው ለኮሪደር ልማት ግብዓቶችን እያቀረቡ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡


 

በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚገኘው የአነጋ ኢነርጂስ ፋብሪካ ባለቤት ፕሮፌሰር ጸጋየ ነጋ በበኩላቸው፤ የንጹህ ማብሰያ እጦት በዜጎች ጤና እና በአየር ንብረት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፋብሪካቸው የሀገሪቱን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ፖሊሲ ታሳቢ በማድረግ ንጹህ የማብሰያ ቁሳቁሶችን እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ ምርቶች ገቢ ምርትን ከመተካት ባለፈ ለውጭ ገበያ ጭምር የሚተርፍ የማምረት አቅም እንዳላቸው የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ በቀጣይ የወጪ ንግድ አቅምን ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።


 

የፋብሪካው ሠራተኞች የሆኑት ገነት ሽዋንግዛው እና ቶልቻ ከበደ በሰጡት አስተያየት፤ ፋብሪካው የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ እናቶች ከጭስና ከድካም የሚገላገሉበትን ቴክኖሎጂ ማቅረቡን ገልጸዋል። 

ሰራተኞቹ በቆይታቸውም ሙያዊ ክህሎታቸውን እያሳደጉና የቴክኖሎጂ ሽግግር እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ መንግስት ለአካባቢ ደኅንነትና ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ አምራቾችን አቅም ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል። 

ከብክለት የጸዳ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማረጋገጥ፣ በታዳሽ ኃይልና በአረንጓዴ አሻራ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም