ባለሃብቶች የአርሶ አደሮችን ህይወት በማሻሻልና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እውን በማድረግ ወሳኝ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባለሃብቶች የአርሶ አደሮችን ህይወት በማሻሻልና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እውን በማድረግ ወሳኝ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ):- ባለሃብቶች የአርሶ አደሮችን ህይወት በማሻሻልና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እውን በማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የተቋማት ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐ-ግብር ባለሀብቶችን በማስተባበር በምዕራብ ሸዋ ዞን ያስገነባቸውን ዘመናዊ ሞዴል ቤቶችን ለአርሶ አደሮች አስረክቧል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የተቋማት ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የተቋማት ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በተለይም በግብርና መስክ የስንዴ ምርታማነትን በማሻሻል የተመዘገበው ስኬት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራም የአርሶ አደሩ ዘመናዊ አኗኗር ዘይቤን እንዲከተል በማደረግ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ሥረዓትን እያሳለጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ ገጠር መስፋፋቱ የአርሶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለው በማንሳት፤ ባለሃብቶችም የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እውን በማድረግ ወሳኝ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ መንግስት በሁሉም ዘርፎች የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት በተጨባጭ እያረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሀብቶችን በማስተባበር በዞኑ ያስገነባቸው ዘመናዊ ቤቶች የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው መስክ የተከናወኑ ተግባራት በሁሉም መስክ ስኬት እያስመዘገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን የዕድገት አቅጣጫ የሚያሳልጡ እመርታዊ ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳርም የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚ ባለሃብቶችን በማነቃቃት በሀገር የዕድገት ጉዞ ላይ አወንታዊ ሚና እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አልሚ ባለሃብቶችም ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር በልማት መስክ ከሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ በተጨማሪ የዜጎችን ህይወት በሚያሻሽሉ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የተሟላ የግብርና ዘይቤን የያዙ ዘመናዊ ሞዴል ቤቶችን በመገንባት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ለአርሶ አደሮች ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ኮሚሽኑ ባለሃብቶችን በማስተባበር የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያሻሽሉ የልማት መስኮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው፣ የገጠር ኮሪደር ልማትን በሁሉም ወረዳዎች በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአርሶ አደሮቹ የተላለፉት ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችና የእንስሳት አያያዝን የሚያሻሽሉ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ናቸው።