ቀጥታ፡

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ኢትዮጵያን የመግለጥ ስራ ማሳያ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ):- የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ፀጋዎችን ገልጦ የማሳየት ስራ አካል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በገበታ ለትውልድ ውጥን የተገነባው እና በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀዋል።


 

ገበታ ለትውልድ ለትውልድ የሚጣል አሻራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ትውልድ ብልጽግናን ሲጎናጸፍ ይህንን ሀውልት እንደ መነሻ ነጥብ የሚያስታውሰው ስራ ነው ብለዋል።


 

ገበታ ለትውልድ የተባለበትና የተመረጡ ስፍራዎች በየአካባቢው ያሉ ታሪኮችና ጸጋዎችን የገለጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ጎርጎራ በጣና ሐይቅ ባሉ ታሪክ ጠገብ አብያተ ክርስትያናት፣ ገዳማት እና መጻሕፍት ያሉበት አካባቢ ገልጦ ለማሳየት ወሳኝ ሚና መጫቱን ተናግረዋል።

ሪዞርቱ በሐይቅ ያለውን አስደማሚ ታሪክ መግለጥ የሚያስችል ስራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የወሎ ህዝብ ያለውን ፍቅር እና ሰላም ወዳድነት አካባቢያቸውን ማልማት እና መቀየር እንዲችል ተጨማሪ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

ማህበረሰቡ ለሚመጣው ትውልድ የለማ፣ ያማረ እና የተትረፈረፈ አካባቢ ጥሎ ለማለፍ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው መንግስት በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በሐይቅ የተከናወነው ድንቅ ስራ በአካባቢው ለሚከናወኑ ቀጣይ ስራዎች ስንቅ በመሆን መጪው ትውልድ የሐይቅ መቀየርን የሚያወሳበት ዘመን ይመጣል ሲሉም ገልጸዋል።

በመልካም ነገር ለመወሳት እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ መልካም ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ እንደ ወሎዬ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍቅር ለመጣ በፍቅር የሚያስተናግድ በፀብ ከመጡበት አጋለይ በማለት በመመከት መመለስ ያውቀበታል ሲሉም ተናግረዋል።

ፀብ ከልማት ፀብ ከብልፅግና ያስተጓጉላል ጉዟችንን ያራዝማል ሲሉም ገልጸዋል።

የምንፈልገው እንደ ወሎዬ በፍቅር የመጣውን አርሂቡ ብለን፤ እጃችንን ዘርግተን ስቀን በፈገግታ መቀበል ማጉረስ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።

ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ነንና ደማችን ውስጥ አለና፤ በፀብ ከመጡብን ደግሞ አጋለይ እንደ ወሎዬ ማለታችን አይቀርም ነው ያሉት።

በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የታየውን መልካም ጅማሮ ለማስፋት በጋራ መስራት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የምንተጋ እና የምንለፋ፣ የምንጓዝበትን መንገድ አንጥረን ለይተን የምናውቅ ለዚያም የምንተጋ መሆን ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም