ቀጥታ፡

መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረትና የሚያደርገው ድጋፍ ለተኪ ምርቶች ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል

ሀዋሳ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰጠው ትኩረትና የሚያደረገው ድጋፍ ለተኪ ምርቶች ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ገለጹ።

ኢንዱስትሪዎቹ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እያመረቱ መሆኑን የሲዳማ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎች ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ6ኛው ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የኢንዱስትሪውን ዘርፉን ለማጠናከር መንግስት የወሰዳቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና መሰል ተግባራት ውጤት ማስገኘታቸውን አንስተዋል።

በዚህም በከፍተኛ ዶላር ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉንና በወጪ ንግድ ላይም ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን መጥቀሳቸውም እንዲሁ።

ኢዜአ በሀዋሳ የኢንዱስትሪ ዞን በመገኘት በተለያየ ዘርፍ ከተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

በዚህም መንግስት ለዘርፉ እያደረገ ባለው ድጋፍ በመታገዝ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በጥራት በሀገር ውስጥ እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በኢንዱስትሪ ዞኑ የስፖርት ትጥቆች እና የብሎኬት ማምረቻ ማሽኖች ምርት ላይ የተሰማሩት አበበ ሀይሉ እንዳሉት ከውጭ በውድ ዋጋ ይገቡ የነበሩ ማሽኖችን በከፍተኛ ጥራት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የመስሪያ ቦታ እና የማምረቻ ማሽን አቅርቦትን ጨምሮ ያደረገው ድጋፍ ለስኬታቸው ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ነው የሚናገሩት።

በመሆኑም ካፒታላቸውን በማሳደግ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውንና ለ16 ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።


 

ከውጭ ይገቡ የነበሩ የቤት ውስጥ መገልገያዎችንና የእንጨት ውጤቶችን በተሻለ ጥራት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑ የገለጹት ደግሞ በእንጨትና ብረታብረት ዘርፍ የተሰማሩት በለጠ ቦላንኮ ናቸው።

መንግስት የሚያመቻቸው የማምረቻ ቦታና የማሽን አቅርቦት እንዲሁም የገበያ ትስስር ለውጤታማነታቸው ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ካፒታላቸውን በማሳደግ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውን አመልክተው ከ60 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረናል ብለዋል።


 

በተለያዩ ማሽኖችን ማምረት ስራ ላይ የተሰማራው ድርጅት ተወካይ ወጣት ዋቅጅራ ጎንፋ በበኩሉ ከዚህ ቀደም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ በመተካት ለገበያ እያቀረቡ እንዳሉ ተናግሯል።

ድርጅቱ አሁን ላይ ወደ 40 ለሚጠጉ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሶ በመንግስት የሚደረገው የማሽን አቅርቦት፣ የገበያ ትስስርና ሌሎች ድጋፎች ለስኬታማነታቸው የላቀ ሚና እንዳለው ገልጿል።


 

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አሻግሬ ጀንበሬ በበኩላቸው፤ በክልሉ ነባርም ሆነ በአዲስ መልክ ወደ ስራ የሚገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ይገኛሉ ብለዋል።

ዘርፉ የስራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚው ላይ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት የማምረቻና መሸጫ ቦታን ጨምሮ የማሽን አቅርቦትና የገበያ ትስስር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ወደ 87 ኢንዲስትሪዎች ያሉ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራትም 137 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን አምርተዋል ነው ያሉት።

በዘርፉ በበጀት ዓመቱ ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ እንዳለም ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን ፀጋ በመለየት የአምራች ኢንዱስትሪውን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ሲሆን ለዚህም በገጠርና ከተማ የኢንዱስትሪ ዞኖችን የማጠናከር ስራ ትኩረት እንደሰተጠው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም