እሴቶችን በመጠበቅና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በማልማት የጋራና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
እሴቶችን በመጠበቅና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በማልማት የጋራና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ዲላ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ በሁሉም አካባቢዎች እምቅ የሆኑ እሴቶችን በመጠበቅና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በማልማት የጋራና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የጌዴኦ የዘመን መለወጫ የዳራሮ በዓል በዲላ ከተማ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር ሰውና ተፈጥሮ ተቻችሎ የመኖር ማሳያ መሆኑን አንስተው "ዳራሮ"ን የመሰሉ እምቅ ሃብቶች የአንድነት፣ የሠላም እና የሀገር ግንባታ እሴቶች ሆነው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
"ዳራሮ" የምስጋና እና የአንድነት በዓል መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ ለሠላም ግንባታና ለህዝቦች ጠንካራ ትስስር የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም እምቅ የሆኑ እሴቶችን በመጠበቅና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በማልማት የጋራና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በክልሉ መልማት የሚችሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች መኖራቸውን አንስተውም በተደመረ አቅም በማልማት ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የተጀመረው ብርቱ ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች በመግለጥና በማልማት የሀገር ሃብት የማድረግ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ባህላዊ እሴቶች በዩኔስኮ እየተመዘገቡና ከሀገር አልፈው የዓለም ቅርስ እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተው "ዳራሮ"ን የመሰሉ እምቅ ሃብቶች መጠበቅና ይበልጥ ማስተዋወቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) የ"ዳራሮ" በዓል አከባበር ከአዲስ ዘመን ብስራትም ባለፈ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የበዓል አከባበሩን ትውፊቶች የቱሪስት መስህብ ከማድረግ ባለፈ በዓለም የማይዳሰሱ ወካይ ቅርሶች እንዲመዘገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።