የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ተገቢውን ህክምና በፍጥነት እንድናገኝ አስችሎናል-ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ተገቢውን ህክምና በፍጥነት እንድናገኝ አስችሎናል-ተገልጋዮች
ሰቆጣ ፤ጥር 30/2018 (ኢዜአ)፡-በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ተገቢውን ህክምና በፍጥነት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለፁ።
ተገልጋዮቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ የነበረው ኋላ ቀር አሰራር ለእንግልት ዳርጓቸው እንደነበርና አሁን ላይ አገልግሎቱ በመሻሻሉ የተቀላጠፈ ህክምና እያገኙ ነው።
በሆስፒታሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ አስረሱ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለፁት የስኳር ህመምተኛ በመሆናቸው በሆስፒታሉ በተደጋጋሚ እየመጡ እንደሚገለገሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የካርድ ክፍልና የጤና መድህን አገልግሎት መስጫ ማእከል ተራርቀው የሚገኙና አሰራሩ የተንዛዛ በመሆኑም ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጸው በዚህም ሳቢያ አገልግሎት ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አውስተዋል።
አሁን ላይ የካርድ ክፍል፣ የጤና መድህንና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎት የሚሰጡ የስራ ክፍሎች በአንድ ማእከል እንዲዋቀሩ መደረጉ ታካሚዎች ያለእንግልት ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም "የህክምና ባለሙያዎች በሰዓቱ አለመግባትና አለመገኘት ይታይ ነበር" ያሉት ታካሚው አሁን ላይ ቁጥራቸው ጨምሮ ያሉትም በሰአቱ በመግባት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሌላው የሆስፒታሉ ተገልጋይ አቶ አያሌው ወልዱ በበኩላቸው አሁን ላይ በሆስፒታሉ ያለው የምርመራና የተኝቶ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለበርካታ ጊዜያት በምልልስ ላይ ቢቆዩም አሁን የሚታከሙበት አልጋ አግኝተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቁመው ሃኪሞችም ተገቢውን ህክምናና እንክብካቤ እያደረጉላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በወሊድ ምክንያት በሪፈር ወደ ሆስፒታሉ በመጣሁበት ጊዜ ተገቢውን እንክብካቤና ህክምና በማግኘቴ የልጅ እናት ለመሆን በቅቻለሁ ያሉት ደግሞ መምህር አልማዝ አስፋው ናቸው።
በህሙማን መተኛና ማዋለጃ ክፍሎች ያለው የጽዳት ሁኔታም በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር ፍጹም መሻሻል በማሳየቱ ደስተኛ ሆነን አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ቢምረው እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍና ለታካሚዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት ተሰርቷል።
ከሆስፒታሉ ሰራተኞች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ መግባባት መቻሉን ጠቁመው የህክምና ክፍሎችንም እንደገና የማደራጀት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህም ከካርድ ክፍል ጀምሮ የተንዛዛውን አሰራር በማስወገድ ታካሚዎች ሳይንገላቱ የሚፈልጉትን የህክምና አገልግሎት በፍጥነትና በጥራት እንዲያገኙ የሚያስችል ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።
በቀጣይም ሆስፒታሉ ለታካሚዎች የተሟላ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖረው እንደሚደረግ ጠቁመው የሲቲ ስካን ማሽን ለማሟላት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።