ቀጥታ፡

ለሰከነ ውይይትና መግባባት ቅድሚያ የሚሰጡ ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ተጨማሪ አቅምን ይፈጥራሉ - ምሁራን

ዲላ፤ ጥር 30/2018 (ኢዜአ) ፡-ለሰከነ ውይይትና መግባባት ቅድሚያ የሚሰጡ ነባር ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ተጨማሪ አቅም ሊሆኑ እንደሚችሉ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ማብራሪያቸው ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን በመለየት የተሻለ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል። 

በቀጣይም በርካቶችን ባካተተ መልኩ አጀንዳዎቹ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ እና ሂደቱም ኢትዮጵያውያን የተቀራረበ ፍላጎት እንዳላቸው በማሳየት ትምህርት የሰጠ መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወሳል። 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን በበኩላቸው ህብረተሰቡ በራሱ ባህልና መልክዓ ምድራዊ አውድ ውስጥ አለመግባባቶችን በሰከነ ውይይት መፍትሄ የማበጀት እሴት ባለቤት ነው ብለዋል።

ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገራዊ ምክክር ስኬት አቅም መሆናቸውን አንስተው የመጠቀም ልምዳችንን ማጎልበት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘላለም ተፈራ እንዳሉት ባህላዊ እሴቶቻችን በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላማዊ ግንኙነትን ያጠናክራሉ።

እሴቶቹ ምቹ የምክክር መድረክን በመፍጠር ለአለመግባባቶች በሰከነ ውይይት መፍትሄ እንደሚያበጁ አንስተው በዚህም የጌዴኦ የ"ጋፌ" ሥርዓት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።  

"በሀገራችን ያሉና ለሰከነ ውይይትና መግባባት ቅድሚያ የሚሰጡ ነባር ሀገር በቀል እውቀቶችን ለምክክር መድረክ ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን አንስተው የመጠቀም ልምዳችንን በማዳበር ለስኬታማነቱ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ መምህር አህመድ ሰይድ በበኩላቸው ሀገር በቀል እውቀቶች በተለይ ስነ ቃሎች የማህበረሰቡ መልካም እሴቶችንና ባህሎችን ለማጎልበት አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ ነው።

በተለይም ለዘላቂ ሠላም መሠረት የሆኑ የጋራ እሴቶች እንዲጎለብቱ በማስቻል ሠላምንና መከባበርን ለማፅናት እንደሚያግዙም ነው የገለጹት።


 

የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ ሥርዓት መሪ አባገዳ ቢፎሚ ዋቆ በበኩላቸው ብሔራዊ የምክክር መድረክ የውይይት ባህላችንን በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በአጀንዳና በተወካይ መረጣ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ "ጋፌ"  ያለምንም ልዩነት እውነትን መሠረት ያደረገ ፍትህን በማውረድ የህዝቡን ሠላም ማስጠበቅ መቻሉን ጠቁመው ባህላዊ እሴቶች ለሃገረ መንግሥት ግንባታና ለሰላም እሴት ያላችውን አበርክቶ በአግባቡ ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።

"ሀገር በቀል የፍትህ ሥርዓት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ዳራሮ 8ኛው ሀገራዊ አውደ ጥናት በዲላ ዩኒቨርስቲ መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም