በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ በመንግስት የስራ ስዓት ላይ ለውጥ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ በመንግስት የስራ ስዓት ላይ ለውጥ ተደረገ
ጋምቤላ፤ ጥር 30 /2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ስዓት ላይ ለውጥ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት፤ የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱና ለስራ አስቸጋሪ በመሆኑ ከፊታችን ሰኞ የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ሰዓት ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል።
የተደረገው የሰዓት ለውጥ ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው በዚሁ መሰረት ሁሉም የመንግስት ተቋማት ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በለውጡ መሰረትም ቀደም ሲል ከጧቱ 1:00 እስከ 6: 30 የነበረው ከ1:00 አስከ 5:30 እንዲሆን እንዲሁም ከስዓት በኋላ ከ9:00 እስከ 11:30 የነበረው 10:00 እስከ 12:30 ይሆናል ብለዋል።
የስራ ስዓት ለውጡ ወይና ደጋ የአየር ንብር ያላቸውን የመንጌሽና የጎደሬ ወረዳዎችን እንደማይጨምር የገለጹት ኃላፊው የክልሉ የመንግስት ሰራተኛች በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቢሮ በመግባት ስራቸውን በትጋት እንዲያከናውኑ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ተወካይ ነብዩ ፈረደ፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ አማካይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 41.4 ድግሪ ሴልሸስ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሌሊቱ ዝቅተኛው የሙቀት መጠን ደግሞ 25 ነጥብ 6 ድግሪ ሴልሸስ መሆኑን ጠቁመው ባለፉት ወራት የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በአማካኝ ከ35 ድግሪ ሴልሸስ የለሊቱ ደግሞ 22 ዲግሪ ሸልሰስ በታች እንደነበር አስታውሰዋል።
በክልሉ የሞቃታማ ወራት የሚባሉት የካቲት፣ መጋቢትና ሚያዚያ ወራት ሲሆኑ በእነዚህ ወራት ውስጥ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እስከ 45 ድግሪ ሴልሸስ የሚደርስበት ጊዜ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።