ቀጥታ፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የበጋ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው

ጭሮ፤ ጥር 30/2018 (ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከ700 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የበጋ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በዞኑ እየተከናወነ ያለውን የበጋ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በተመለከተ ኢዜአ የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎችና የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮችን አነጋግሯል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ ሸረፍ አብደላ፤ በዞኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በተለይም ተራቁተው የቆዩ ተራራማ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

በልማቱ የተገኘውን ውጤት ተከትሎ በበጋና ክረምት ጭምር የልማት ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን አንስተዋል። 

በዚህም መሰረት በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ700 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ455 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በልማቱ እስካሁን ከ109 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር በላይ የአፈርና የድንጋይ እርከን ስራ በማከናወን የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካት የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ጀማል አብዶ፣ ወይዘሮ ነስራ አብዱሬ እና አብነት ጉልላት፤ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራው አካባቢን ከመጠበቅም ባለፈ ለምርታማነት መጨመር ትርጉም ያለው በመሆኑ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።


 

የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን ከማሳደግም ባለፈ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ተናግረው አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም