የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በምዕራብ ሸዋ ዞን ያስገነባቸውን ዘመናዊ የገጠር ሞዴል ቤቶች ለአርሶ አደሮች አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በምዕራብ ሸዋ ዞን ያስገነባቸውን ዘመናዊ የገጠር ሞዴል ቤቶች ለአርሶ አደሮች አስረከበ
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብር ባለሀብቶችን በማስተባበር በምዕራብ ሸዋ ዞን ያስገነባቸውን ዘመናዊ ሞዴል ቤቶች ለአርሶ አደሮች አስረክቧል፡፡
በምረቃና ርክክብ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ቤቶቹ መንግሥት የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ በልዩ ንድፍ የተገነቡ ናቸው።
ዘመናዊ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የተገጠመላቸው፣ ምግብ ለማብሰል ባዮጋዝ የሚጠቀሙ፣ ሙሉ መገልገያዎችና ዘመናዊ መፀዳጃ ቤት እና የተሟላ ሰርቪስ ቤቶች ያሏቸው ናቸው።
የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ባገናዘበ መልኩ የተለየና ንጽህናው የተጠበቀ የእንስሳት በረት የተሰራላቸውም ናቸው፡፡
የቤት ግንባታ ፕሮጀክቱ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል ሲሆን መንግሥትን ተግባራዊ እያደረገ ያለውን የገጠር አኗኗርን የማሳደግ ራዕይ በተግባር ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ከመርዳት ባለፈ የልማት ስራዎችን ወደ ገጠር መንደሮች በማስፋፋት ረገድ ትልቅ እመርታ እያሳየ እንደሚገኝ በመርሃ ግብሩ ላይ ተመልክቷል።