በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተግኝቷል
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የቡና ዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
በቡና ዘርፍ እየተመዘገቡ ላሉ ውጤቶች በርካታ ስትራቴጂዎች፣ የምርታማነትና ጥራት ማደግ፣ የገበያ አድማስ ማስፋት እንዲሁም ዲጂታላይዜሽንና ዘመናዊ አሰራሮች መተግበራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በምርት መጠንና በጥራት ላይ የተከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተፈላጊነት ማሳደጋቸውን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ቡና የምትልክባቸውን ሀገራት ቁጥር ወደ 84 ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል።
በተለይም በምስራቅ እስያ ባሉ ገበያዎች በስፋት ለመሳተፍ የተደረጉ የማስተዋወቅ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ አጠቃላይ የቡና ግብይት ሂደቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ በስፋት እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ዘርፉን ለማዘመን እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል እያንዳንዱ የቡና ምርት ከየት ጣቢያ እንደመጣ፣ የት መጋዘን እንደገባ እንዲሁም ማን እንደላከው መከታተል የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ይህም የምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ የምርቱን ደህንነትና ጥራት ለማረጋገጥ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 600 ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ ሦስት ቢሊየን ዶላር ለማግኘት አቅዶ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አቶ ሻፊ አመልክተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት 200 መቶ ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 345 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 469 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወቃል፡፡