ቀጥታ፡

በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ

ደሴ፤ ጥር 30/2018( ኢዜአ)፡- በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ክንውን የምርጫ ቦርድን ህግና አሰራር በማክበር ለመፎካከር ለእጩዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ከወዲሁ ግንዛቤ መፍጠራቸውን ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ እለት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ. ም የሚካሄድ ይሆናል።

ለምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ፉክክር ቦርዱ ለፓርቲዎች እኩል የመወዳደሪያ እድሎችን በመፍጠር ከእጩዎች ምዝገባ ጀምሮ ዜጎች ድምፃቸውን ለመስጠት የምርጫ ካርድ የሚወስዱበትን ቀልጣፋ አሰራር ዘርግቷል።

በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን በማስመዝገብ ለውድድሩ የተሟላ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኢዜአ በደሴ ከተማ ካነጋገራቸው ፓርቲዎች መካከል የወሎ ዴሞክራቲክ ፓርቲ፤ የኢዜማ እና ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በምርጫው ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። 

የወሎ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ዳውድ መሀመድ፤ ፓርቲያቸው ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊነት የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ብቁ የሆኑ እጩዎችን በማስመዝገብ ፓሊሲና ስትራቴጂያቸውን ለህዝብ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።

በኢዜማ ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዳኜ ሰብስቤ፤ የዘንድሮው የምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ ጥሩ የዴሞክራሲ መሰረት የሚያሲዝ ታሪካዊ ሆኖ እንዲካሄድ የፓርቲዎች ዝግጁነትና ቀና ትብብር መሆኑን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረትም ኢዜማ ለምርጫው መሳካት የድርሻውን ለመወጣትና ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የህዝብ ድምፅ ለማግኘት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉ ብቁ የሆኑ እጩዎችን እያስመዘገበ መሆኑን አንስተው ለምርጫው መሳካት በተለይም የፖለቲካ ተዋናዮች ሃላፊነት ወስደን መስራት ይገባናል ብለዋል።  

በብልፅግና ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ አለማየሁ፤ ከለውጡ በኋላ በተፈጠረው ፍትሃዊና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር በመጠቀም ፓርቲዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።

ከዚህ አንፃር ብልፅግና ፓርቲ ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሂደት ፓርቲያቸው የላቀ ሚናውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በምርጫው ሀገርና ህዝብን በብቃት ማገልገል የሚችሉ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን እጩዎች በማስመዝገብ ለውድድሩ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ግልጽ እና ተዓማኒ ለማድረግ የተሟላ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱን መግለጹ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም