ለሀገራዊ ምክክሩ ቀሪ ሥራዎች መሳካት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን-የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ቀሪ ሥራዎች መሳካት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን-የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ፤ ጥር30/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ ቀሪ ሥራዎች መሳካት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ሲል የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ "ምክክር ልብን ያሳርፋል፤ ውይይትም ስብራትን ይጠግናል" ሲሉ የምክክርን ፋይዳ አስረድተዋል።
የአሁኑ ትውልድም ቅድመ አያቶቹ ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት የከፈሉትን የጀግንነት ወኔ በመላበስ፣ በሰለጠነ የምክክር አውድ የተሰራች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ማወያየቱን ጠቅሰው፤ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በርካታ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ገልጸው፣ እስካሁን የአጀንዳ ማሰባሰብና በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ መስኡድ አደም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የችግሮች ዘላቂ መፍቻ በመሆኑ ለስኬቱ በጎ ሚና ማበርከት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን በየክልሉ ከወረዳ ጀምሮ አጀንዳ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ሃሳቦችን ማሰባሰቡና ተሳታፊዎችን በመለየት ችግሮችን በምክክር ለመፍታትና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል መሰረት መጣሉን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በማካሄድ ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ደረጃ በተከናወኑ መድረኮች ላይ ተወካዮች እንዲመረጡ በማድረግ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ ቀሪ ስራዎች መሳካት ጉባኤው ሚናውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ጠቀሜታው ለሀገር በመሆኑ ወደ ሂደቱ ያልገቡ አካላት በሀገራዊ ምክከሩ እንዲሳተፉና አጀንዳዎቻቸውን በማቅረብ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።