ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ አርሰናል ከሰንደርላንድ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ጥር 30 /2018 (ኢዜአ)፦  በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በዚህም መሠረት ምሽት 12 ሰዓት ላይ አርሰናል ሰንደርላንድን በኤምሬትስ ስታዲየም ያስተናግዳል።

አርሰናል በ53 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ሰንደርላንድ በ36 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።

መድፈኞቹ በ24ኛው ሳምንት ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ 0 በማሸነፍ ከሶስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል።

አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ ዘጠነኝ ከፍ ያደርጋል።

ሰንደርላንድ በ24ኛ ሳምንት በበርንሌይ ካሸነፈበት ጨዋታ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ29 ነነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ መነቃቃትን ያሳየው ማንችስተር ዩናይትድ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታል።

ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ወደ ማሸነፍ መንገድ ለመመለስ ይፋለማል።



ዎልቭስ ከቼልሲ፣ ቦርንማውዝ ከአስቶንቪላ፣ ፉልሃም ከኤቨርተን እና በርንሌይ ከዌስትሃም ዩናይትድ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።



ኒውካስትል ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በሴይንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም