በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ዘላቂና አካታች ልማትን የሚያረጋግጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ዘላቂና አካታች ልማትን የሚያረጋግጡ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ዘላቂና አካታች ልማትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ገለፁ።
3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ተጠናቋል።
በጉባኤው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በጉባኤው ሃሳባቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላት እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ተግባራት በከተማዋ ዘላቂና አካታች ልማትን የሚያረጋግጡ ናቸው።
እነዚህ ተግባራት የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን ያለሙ መሆናቸውን አባላቱ አመልክተዋል።
አስተዳደሩ ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰፋፊ ሥራዎችን ያከናወነበትን ሂደት የምክር ቤት አባላቱ አድንቀዋል።
በተለይም ዘመናዊ የኪነ-ጥበብ መድረኮች፣ የአምፊ-ቲአትሮችና ደረጃቸውን የጠበቁ የሲኒማ ቤቶች ግንባታ በተሻለ መልኩ መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ የጥበብ ማዕከላት ለከተማዋ የባህል ገጽታ ግንባታ፣ ለትውልድ ቀረጻ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ለሚያጠናክሩ የጋራ ትርክቶች መገንቢያ መሆናቸውንም አክለዋል።
በመዲናዋ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል የሚያገለግሉና አካታች የሆኑ ተቋማት መገንባታቸውን የጠቀሱት አባላቱ፤ እነዚህ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በፕሮጀክት አፈፃፀምና በገቢ አሰባሰብ የተገኙ ውጤቶች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ የተከናወኑት የልማት ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ማረጋገጥ ያስቻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተከናወኑት የልማት ተግባራት ሁሉ ጥናትን መሰረት ያደረጉና ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል።
ስራዎቹ አዲስ አበባ እንደ መዲናነቷ ሊኖራት የሚገባውን የከተማነት መስፈርትና ደረጃ የሚያሟሉ መሆናቸውንና በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ግባችን ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ አዲስ አበባ የብልፅግና ማሳያና ማዕከል እንድትሆን በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በተጨማሪም የ33 የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የሰባት የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።