ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምክክሩን ስኬታማ የሚያደርጉና በአርዓያነት የሚጠቀሱ ተግባራትን አከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምክክሩን ስኬታማ የሚያደርጉና በአርዓያነት የሚጠቀሱ መጠነ ሰፊ ተግባራት ማከናወኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ። 

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የሥራ አፈጻጸም እና የቀጣይ ዕቅዶችን ገምግሟል። 


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እውነቱ አለነ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩ ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ስልጡን የፖለቲካ ባሕል በማስፈለጉ የምክክር ኮሚሽኑ ተቋቁሟል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ መጠነ ሰፊ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸው የሂደቱ አሳታፊነትና አካታችነት ለሌሎች ሀገራት ጭምር ትልቅ ልምድ ሊሆን የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። 

በሂደቱ ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት አባዜ ቀርቶ፣ በምክክርና በሀሳብ የበላይነት ወደሚመራ ስልጡን የፖለቲካ ባህል መግባት መጀመሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ በብልሃትና በጥንቃቄ ባከናወናቸው ተግባራት እስካሁን በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብና ለዋናው ጉባኤ የሚሳተፉ ሰዎችን የማስመረጥ ሥራ በስኬት ማከናወኑ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህ ተግባር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕዝቡ በምክክሩ ትልቅ ተስፋ መሰነቁን ጠቅሰው ቀሪ ሥራዎችን ለማሳካት ሁሉም ሚናውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

በትግራይ ክልል የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ማፋጠን እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ሰብሳቢው ጥሪ አስተላልፈዋል።


 

የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ በበኩላቸው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አመርቂ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የምክክሩና የአጀንዳው ዋና ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ የሁሉንም ሕዝብ ተሳትፎ በማረጋገጥ በኩል ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ዋናው የምክክር ጉባኤ ለመግባት አመቻቾችንና አወያዮችን በፍጥነት የማሰልጠን ሥራ በትኩረት ሊከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፥ የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም አካታችነትን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።


 

እስካሁን ባለው ሂደት ከ1ሺህ 234 ወረዳዎች አጀንዳዎችን የማሰባሰብና ለዋናው ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራ በስኬት መከናወኑን ገልጸዋል።  

በተጨማሪም ከ38 የፌዴራል ተቋማት፣ ማኅበራት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎች ተሰብስበው የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ኮሚሽኑ የሥራ ሂደቱን ለማቀላጠፍ የአሠራር ሥርዓቱን በዲጂታል የታገዘ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ሀገራዊ አጀንዳዎችን ማጽደቅ፣ እጅግ መሠረታዊ የሚባሉ አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፣ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ማጠናቀቅ እና ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ማካሄድ በቀጣይ በትኩረት የሚከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም