ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የምዘና እና ፈተና ሥርዓቱን ማዘመን ላይ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የምዘና እና የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን ለማዘመን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።

“ከተለዋዋጭ ዓለም ጋር የተጣጣመና ምላሽ የሚሰጥ የምዘና ሥርዓት መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ 3ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ የትምህርት ምዘናና ፈተና ጉባኤ የዘርፉ ተዋናዮች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።


 

በጉባኤው በምዘናና ፈተና አተገባበር ዙሪያ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችንና ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ 25 ልዩ ልዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ይቀርባሉ።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የምዘና ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ማዘመን የሚያስችሉ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንደገለጹት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ትምህርት ቁልፍ መሣሪያ ነው። 

በመሆኑም የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፎችንና አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለማከም መንግሥት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ መደገፍና ማዘመን ቀዳሚው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የፈተናና ምዘና አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማሸጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ጉባኤው በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታትና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።


 

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ ተቋሙ ለትምህርት ጥራት መሻሻል፣ ለምዘና ሥርዓቱ መዘመንና ብቁ ዜጋን ማፍራት የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎች እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

ቀደም ባሉ ዓመታት የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸው፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለትምህርት ዘርፉ ውጤታማነት በግብዓትነት እንዲያገለግሉ መደረጉን አመልክተዋል።


 

በጉባኤው ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) ዓለም የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ለመድረስና በፍጥነት ለመራመድ የምዘና ሥርዓታችንን ዘመኑን የዋጀ ማድረግ የግድ እንደሚል ገልጸዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ግሩም ታረቀ(ዶ/ር) እና ጀማል አብዱል ቃድር(ዶ/ር) በበኩላቸው መሰል ትምህርታዊ ጉባኤዎች ምሁራን ዕውቀታቸውንና የምርምር ግኝቶቻቸውን ለማካፈል እንደሚያስችሉ አንስተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም