ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር የካቲት 1 ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር የካቲት 1 ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር ከየካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ
ውድድሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ውድድሩ "የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ ይከናወናል።
ሚኒስትር ዴኤታው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድሩን ለማከናወን አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
መንግስት የስፖርት ልማት ሥራዎችን ከስፖርት መሰረተ ልማት አንስቶ በታዳጊ ልማት እና በብሄራዊ ቡድን ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በያዘው እቅድ መሠረት ታዳጊዎችን በስልጠና ማዕከላትና በአካዳሚ መልሶ በማደራጀት የስልጠና አሰጣጥ ሂደትን የማዘመንና የመፈተሽ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ይህን መነሻ በማድረግ የዘንድሮው የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር በአዳማ ከተማ ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ታዳጊዎችን በአንድ ማዕከል ላይ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ለማድረግ ውድድሩ የላቀ ድርሻ እንዳለው ተመላክቷል።
ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር የአትሌቶች የስልጠና ሂደት የሚመዘንበት፣ ተሞክሮ የሚወሰድበት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
ተተኪ ስፖርተኞች የሚመለመሉበት ውድድር ከ15 ዓመት በታች አትሌቶች የሚወዳደሩበት መሆኑ ከባለፉት ዓመታት ለየት እንደሚያደርገው በመግለጫው ወቅት ተነስቷል።
በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር ሶስት ሺህ የስፖርት ልዑካን እንደሚሳተፉና በ15 የስፖርት አይነቶች ውድድሩ እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።
ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።