ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እያገዘ ነው

አጋሮ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እያገዘ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) ገለጹ።

የአጋሮ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ በይፋ ስራ ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መድረኩ የተገኙት ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር)፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በየአካባቢው ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እያገዘ ነው ብለዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ የመልካም አስተዳደር ችግርን ትርጉም ባለው መልኩ መፍታት እያስቻለና በተለይም የህዝቡን እንግልት ለመቀነስና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ሕዝቡ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ነው።

ከእነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው እስካሁንም በሸገር፣ በአዳማ፣ በጅማ፣ በቢሾፍቱ እና በሻሸመኔ ከተሞች መጀመሩን አስታውሰዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀድሞ በተጀመረባቸው ከተሞች አገልግሎቱ የበለጠ እየሰፋ ወደ ክፍለ ከተሞችም እየወረደ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጋሮ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ስራ መጀመር በከተማ አስተዳደሩ ሲነሳ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአጋሮ ከተማ ከንቲባ ነዚፍ መሀመድ አሚን ናቸው።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም