ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን የመጀመሪያ ዙር በድል አጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን የመጀመሪያ ዙር በድል አጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የአማካይ ተጫዋቹ ኤርሚያስ ሹምበዛ በ14ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
አቡበከር አዳሙ ከኢትዮጵያ ቡና፣ መልካሙ ቦጋለ ከወላይታ ድቻ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።
ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና በ23 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 12ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ ሰባተኛ ሽንፈትን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ወላይታ ድቻ ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቋል።
የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ዙር መርሐ-ግብር የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጀመር የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።