ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል

አርባ ምንጭ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ተግባራት በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግማሽ ዓመቱ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ ከቱሪዝም ቢሮ ሃላፊዋ ወይኒቱ መልኮ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የቢሮ ኃላፊዋ እንዳሉት በክልሉ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን ጨምሮ እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችና ብሔራዊ ፓርኮች ይገኛሉ።

እነዚህን የቱሪዝም ሀብቶች ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል

በዚህም መስህቦቹን በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

በግማሽ ዓመቱ 5 ሚሊየን 626 ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የክልሉን የመስህብ ስፍራዎች እንደጎበኙና ከዚህም ከ710 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት ለ4ሺህ 658 ዜጎች በቀጥታ እንዲሁም ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ በተዘዋዋሪ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አስረድተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ አስጎብኚዎች መካከል በአርባ ምንጭ የሚገኘው የታሪክ ሪፍት ቫሊ ቱር ስራ ማኔጀር ወጣት ታሪኩ ቶሌራ የክልሉን የቱሪዝም ፀጋዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ለማስተዋወቅ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።

በክልሉ እምቅ የቱሪዝም ፀጋዎችና አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ እንዲሁም የማህበረሰቡ እንግዳ ተቀባይነት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሷል።

ለዚሁም እንግዶችን የሚያስተናግዱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጆች፣ ሪዞርቶችና ሆቴሎች በስፋት መኖራቸውም የቱሪስቶችን ቆይታ ጊዜ እንዲጨምር አድርጓል ብሏል።

በክልሉ ቱባ ባህል፣ መልክአ ምድሮች፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች፣ አስደናቂ ታሪካዊ ስፍራዎች መኖራቸውን መመልከታቸውን የገለጹት ደግሞ ከጎብኚዎች መካከል አሜሪካዊቷ ኤልሳቤጥ አፈሳ ናቸው።

በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን ጠቁመው ወደ አሜሪካ ሲመለሱ ሌሎች ቤተሰቦቼና ወዳጆቼ መጥተው እንዲጎበኙ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም