የቀበሌ አደረጃጀቱ አገልግሎት በቅርበት ለማግኘትና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቀበሌ አደረጃጀቱ አገልግሎት በቅርበት ለማግኘትና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው
መቱ፣ጥር 29 (ኢዜአ)፡-በኢሉአባቦር ዞን ከዓመት በፊት ወደስራ በገባው የቀበሌ አደረጃጀት አገልግሎት በቅርበት ማግኘት ከማስቻል ባለፈ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው ሲሉ በመቱ ወረዳ የእሁድ ገበያ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በኢሉአባቦር ዞን 287 ቀበሌዎች በአዲስ መልክ ተዋቅረው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ቀበሌዎቹም ለህዝቡ በቅርበት እያገለገሉ መሆኑ ተመልክቷል።
በዞኑ መቱ ወረዳ የእሁድ ገበያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ታደሰ የቀበሌ አደረጃጀቱ ወደስራ ከገባ ወዲህ የሚፈልጉትን አገልግሎት በቅርበት እያገኙ ነው።
ከዚህ በፊት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ወረዳ ማዕከል ለመሄድ ከሚያወጡት ወጪና ድካም መቅረቱን ገልጸው አሁን ላይ ግዜያቸውንም በአግባቡ ለልማት ስራ ማዋል እንደቻሉ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ መንግስት ለልማት ጥያቄዎቻቸው ትኩረት እንዲሰጥ እድል መፈጠሩንም ተናግረዋል።
አቶ ጀማል አብደላም የቀበሌ አደረጃጀቱ የሚፈልጉትን የመንግስት አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የልማት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ እያገዘ ነው።
በተለይ በወረዳ ደረጃ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ተገልጋዮች የሚበዙባቸው መሆኑን ተከትሎ ምልልስና ቀጠሮዎች ይበዙበት እንደነበር አስታወሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት የሚቀረጹ የልማት ፕሮግራሞችና የስራ አቅጣጫዎች በወቅቱ ሕብረተሰቡ ጋር እንዲደርስ በማስቻል ለልማት እያነሳሳቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በመቱ ወረዳ የእሁድ ገበያ ቀበሌ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ፍጹም ባሕሩ እንደተናገሩት አዲሱ በቀሌ አደረጃጀት ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እያስቻለ ነው።
በዚህም አገልግሎቱ ሕብረተሰቡ ጊዜውን በልማት ላይ በማዋል ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን ኑሮውን ለማሻሻል እያገዘ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የኢሉአባቦር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞሲሳ ለሜሳ ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በዞኑ 287 ቀበሌዎች ለሕብረተሰቡ በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሰፍን አግዟል ብለዋል።