ወጣቶች በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገት ላይ ያላቸውን አበርክቶ እንዲያጎለብቱ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገት ላይ ያላቸውን አበርክቶ እንዲያጎለብቱ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ድሬዳዋ፣ ጥር 28/2018 (ኢዜአ) ፡-ወጣቶች በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገት ላይ ያላቸውን አበርክቶ እንዲያጎለብቱ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የአፍሪካ ቀንድ አገራት ወጣቶች በቀጣናው የጋራ ዕድገት እና ዘላቂ ሰላም ላይ የተቀናጀ አበርክቶ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችላቸው የድሬ-ፎረም ጉባኤ ነገ በድሬደዋ ከተማ መካሄድ ይጀምራል።
የድሬ ፎረም ሁለተኛ ጉባኤን በማስመልከት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ለመገናኛ ብዘሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ላይም ሁለተኛው የድሬ ፎረም ጉባኤ " የአፍሪካ ቀንድ አገራት ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም እና አየር ንብረት ለውጥ ሚና " በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በጉባኤው በሚነሱ ሐሳቦች ወጣቶች አሻጋሪ የሆኑ ሃሳቦችን በማመንጨት ለቀጠናው የጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት የድርሻቸውን ለመወጣት የሚስችላቸው መደላድል ይፈጥሯሉ ተብሏል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎና አደረጃጀት አቅም ግንባታ ኃላፊ አቶ አድነው አበራ፤ በወቅቱ እንዳሉት፣ ወጣቶች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ወጣቱ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በአፍሪካ አህጉርና በዓለም አደባባዮች የመሪነት ሚናውን እንዲያሳድግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ወጣቶች ከሀገራቸው ባለፈ ለአህጉሪቱ አሻጋሪ ሃሳቦች በማመንጨት ሁለንተናዊ የጋራ ዕድገት እንዲመዘገብ የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ በየመስኩ የተመቻቸ ምህዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ በበኩላቸው፤ ነገ በሚጀመረው ጉባኤ ኢትየጵያ በአፍሪካ ቀንድና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ስራ እያከናወነች ባለችው ስራና ቀጣይነት ላይ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በቀጠናው ዘላቂ እና የተቀናጀ ዕድገት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የከፍታ ሚና ወጣቶች ተቀናጅተው የድርሻቸውን እንዲወጡ መደላድል ለመፍጠር ጉባኤው ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ።
እንደ አገር የተጀመረውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ በሆነው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይጋለጥ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ ተሞክሮዎችን በማቅረብ በቀጠናው እንዲስፋፋ ፎረሙ ወሳኝ ሚና ያበረክታል ብለዋል።
ወጣቱ በቀጣናው የተሻለ ሰላም፣ ዕድገት እና የጋራ ብልፅግንና ለማረጋገጥ አንዲችል የጋራ ፎረም አዘጋጅተን ጉዞ ጀምረናል ያለው ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ሰብሳቢ ወጣት ሃሚድ አብደላ ነው።
ነገ በሚጀመረው የድሬ ፎረም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ወጣቶች ጉባኤ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ፣ የሁሉም ክልሎች የወጣት ተወካዮች ፣ ምሁራን እና ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።