በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ማስተማር ስራን ለማሳካት ለመምህራን ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ማስተማር ስራን ለማሳካት ለመምህራን ልማት ትኩረት ተሰጥቷል
አርባ ምንጭ፣ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ማስተማር ስራን ለማሳካት ለመምህራን ልማት ትኩረት መስጠቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለሚያስተምሩ የአንደኛ ደረጃ መምህራን የክህሎት ስልጠና በአርባ ምንጭ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናውን አስመልክተው የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ዘርፍ ሃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ ታምራት ይገዙ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መከታተላቸው አካባቢያቸውንና የትምህርት ይዘቶችን በአግባቡ የሚረዱበትን እቅም ያሳድጋል።
ይህን ለማሳካትም በአፍ መፍቻ የሚያስተምሩ መምህራን አቅም በማሳደግ የመማር ማስተማር ስራውን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአሁኑ ስልጠናም በዘርፉ ያለውን የመምህራን እጥረትን ለመፍታት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የተማሪ መጻሕፍትና የመምህሩ መምሪያ እጥረቶችን ለመፍታት መስራቱ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና የፈተና ስርዓትን በማዘመን የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አስተባባሪው አስረድተዋል።