ቀጥታ፡

ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎች ማሰባሰብ እና ልየታ ላይ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎች ማሰባሰብ እና ልየታ ላይ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቃባይ ጥበቡ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በምክክርና በሰለጠነ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

ይህም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ከፍተኛ አበርክቶ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ኮሚሽኑ ሁሉን አሳታፊና አካታች መርህን በመከተል የሁሉም ድምጽ የተሰማበት ውጤታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

በፌደራል ደረጃ፣በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከዳያስፖራው ማኀበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ መቻሉን አብራርተዋል።

አጀንዳ ልየታ ላይም በተመሳሳይ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፥ በዋናው ምክክር ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችም መለየት መቻሉን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ፥ የምክክር ኮሚሽኑ እስከ አሁን በመጣበት ሂደትና በፈጠራቸው መድረኮች የምክክሩ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የሚችሉበት ምቹ አውድ ተፈጥሯል።

የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶች መንስዔ የሆኑ ጉዳዮች በውይይትና በምክክር በመፍታት የተሻለች ሀገር መገንባት እንደሚቻል ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም