የለውጡ መንግስት በአካባቢው ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቁ የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን እየመለሰ ነው - የጉጂ አባ ገዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግስት በአካባቢው ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቁ የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን እየመለሰ ነው - የጉጂ አባ ገዳዎች
ሻኪሶ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት በአካባቢው ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቁ የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን እየመለሰ መሆኑን የጉጂ አባ ገዳዎች ገለጹ።
ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት የሻኪሶ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።
በዚሁ ጊዜ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው አባ ገዳዎች ቀደም ባሉት ዓመታት የጉጂ ህዝብ በርካታ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንደነበሩበት አንስተዋል።
በዚህ ምክንያት ህዝቡ አንገብጋቢ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመንግስት አካላት በተከታታይ ሲያቀርብ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ከለውጡ ወዲህ ግን መንግስት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸውን እየመለሰ፣ አካባቢውንም የልማት ማዕከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የጉጂ አባገዳ የሆኑት አባ ገዳ ገናሌ አጋ፣ በአካባቢያችን ሲጠየቅ የቆየው የልማት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ በመሆኑ ተደስተናል ብለዋል፡፡
አካባቢው በወርቅና በሌሎች ማዕድናት እንዲሁም በቡና ሀብት የታደለ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ሀብት ለማልማት መሰረተ ልማት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሻኪሶ አየር ማረፊያ ግንባታ መጀመር ለዘመናት ምላሽ ሳያገኙ የቆዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ተራ በተራ ምላሽ እያገኙ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑንም አክለዋል።
እየተከናወነ ያለውን የልማት ሥራ እንዲሁም ሠላሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ድርሻውን እንዲወጣ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል።
ሌላው የአካባቢው አባ ገዳ የሆኑት ገዳ ጉዬ በበኩላቸው የሻኪሶ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር እና ሌሎች በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች መንግስት አካባቢውን ለማልማት የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ብለዋል።
የለውጡ መንግስት አካባቢውን ለማልማት የጀመረው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡን በማስተባበር ሚናቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል።
የአየር ማረፊያው ግንባታ ሲጠናቀቅም አካባቢውን በንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡