ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና በብቁ ባለሙያዎች የታገዘ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠች ነው- የውጭ ሀገራት ዜጎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና በብቁ ባለሙያዎች የታገዘ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠች ነው- የውጭ ሀገራት ዜጎች
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና በብቁ ባለሙያዎች የታገዘ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠች መሆኑን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ገለጹ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በህግ የተሰጠውን የድንበር ቁጥጥር ለማከናወን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ድንበር ቁጥጥር ሥራ ያከናውናል፡፡
የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ዓለም አቀፍ ህግና አሰራርን ተከትለው በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፤ ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እንግዶችን ለመቀበል ያደረገውን ዝግጅትም አስጎብኝቷል፡፡
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመዳረሻ ቪዛ ሲቀበሉ ያገኘናቸው ጋናዊቷ ማቪስ አኒማ ቦንሱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መስጫ መስኮቶች ጥቂት ተገልጋዮች ደግሞ ብዙ ነበሩ ብለዋል፡፡
በዚህ ምክንያት "ከአውሮፕላን እንደወረድኩ ሰልፍ ለመያዝ እየሮጥኩ ነበር የመጣሁት" ያሉት ማቪስ አኒማ ነገር ግን የጠበቃቸው በፈገግታ የሚያስተናግዱ ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ስምጣ ስርዓቱ ሁሉ ተቀይሯል፤ የቪዛ አገልግሎቱ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂና የላቀ አገልግሎት በሚሰጡ ባለሙያዎች ተሞልቷል ብለዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ትልቅ አድናቆት እንዳላቸው የገለጹት ማቪስ አኒማ፤ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የመዳረሻ ቪዛ ሲወስድ ያገኘናቸው ብራዚላዊው ፔድሮ ላካዝ አማራል በኢትዮጵያውያን ፈጣን የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ ተድንቄያለሁ ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ቪዛ እንዳልነበራቸው ገልጸው፤ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ዶክመንቶቻቸውን አረጋግጠው የመዳረሻ ቪዛ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡
"የተጠየኩት የግብዣ ደብዳቤና ፓስፖርቴን ነው፤ ባለሙያዎች በፈገግታ ነው የሚያስተናግዱ ቅንና መልካሞች ናቸው" ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ባለደረባና የሌሴቶ ዜግነት ያላቸው ማምዌላዝ ኮማ የኢትዮጵያ የኢሚግሬሽን አገልግሎት አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው መሆኑን በመግለጽ፤ የተደረገልኝ አቀባበል ኢትዮጵያዊ እንደሆኑኩ ተሰምቶኛልና በተደጋጋሚ መምጣት እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡
የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑን "የቢዝነስ ክላስ" እንደሚመስል በመግለጽ፤ ኢትዮጵያውያን ቀናኢና እንግዳ ተቀባዮች በመሆናቸው ሁሉም ሰው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እመክራለሁ ብለዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ካናዳዊት ሂሩት አሰፋ፤ ኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ስትሰጥ በማየቴ ኩራት ተሰምተኛል ብለዋል፡፡
የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ለማግኘት መሰለፍ አይጠበቅብንም፤ ምክንያቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጡ ብዙ ባለሙያዎች አሉ ብለዋል፡፡
ባለሙያዎች ፈጣኖች መሆናቸውን ገልጸው፤ ማንኛውንም ጫና ተቋቁመው ሰዎችን በብቃትና በፍጥነት ያስተናግዳሉ ብለዋል፡፡