የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ምእራብ አርሲ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ) ፡- በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል ምእራብ አርሲ ዞን ናንሰቦ ወረዳ የናንሰቦ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በይፋ ተመርቋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የነንሰቦ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ 824 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እያደገ መምጣቱን ነው የሚናገሩት።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው ፕሮጀክቶቹ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ የአካባቢው ህዝብ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሬክተር ኢንጅነር ጥላሁን ብርሃኑ፤ አገልግሎቱ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 8 ሺህ 400 በላይ ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀት ላይ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ደግሞ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን የማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም ከ 5 ሺህ 137 በላይ ደንበኞች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
የነንሰቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባሪሶ ባሜ በበኩላቸው፤ ከፍተኛ የልማት ፍላጎትና ሃብት ያለው የወረዳው ህዝብ የቆየ የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄው እየተመለሰ ነው ብለዋል።
የፌደራልና የክልል መንግስታት ቁርጠኛ አቋም በመያዝም የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ያከናወኑት ተግባራት ለአካባቢው እድገት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አባገዳ ጣሂር ጎዳና በበኩላቸው፤ መንግስት የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረው የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የህዝቡን ህይወት መቀየሩን ገልጸዋል።
በዚህም የለውጡ መንግስት ሊመሰገን ይገባል ያሉት አባገዳው የአካባቢው ህብረተሰብ የፀሐይ ኃይል ማመንጫው ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ተገቢውን ጥበቃ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።