መገናኛ ብዙሃን መጪው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የሕዝብን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን መጪው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የሕዝብን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል
ሳውላ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን መጪው ምርጫ ስኬታማና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዜጎችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራን አስታወቁ።
ምርጫ ዜጎች የሚበጃቸውንና ሀገርን በተገቢው መንገድ ያስተዳድራል ብለው ያመኑበትን ወደ ስልጣን የሚያመጡበት፤ አይበጀኝም ያሉትን ደግሞ በካርዳቸው የሚጥሉበት ብቸኛው መንገድ ነው።
ኢዜአ ማሕበረሰቡ በምርጫው ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ መገናኛ ብዙሃን በሚኖራቸው ሚና እና ኃላፊነት ዙሪያ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተመስገን መነሻ እንዳሉት፤ መራጩ በዕውቀት ላይ ተመስርቶ በመርጫው ተሳታፊ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል።
በተለይ ዜጎች በቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ወቅት ያሉትን ሂደቶች እንዲገነዘቡ ከማድረግ አንፃር ቦርዱ የሚያወጣውን መርሃ ግብር በአግባቡ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለመወዳደር ይዘው የቀረቡትን አዲስ ነገርና ማኒፌስቶ በማስተዋወቅ፣ የፓርቲዎችን አላማና እቅድ ህዝቡ እንዲረዳቸው ከማድረግ አንፃር መገናኛ ብዙኃን በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በተለይም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነት በመፈተሽ መራጩ ሕዝብ ተገቢ የሆነ መረጃ እንዲደርሰው ከማድረግ አኳያ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው መምህር አባዲ ካህሳይ መገናኛ ብዙሃን ፓርቲዎች በምርጫ ህግና ደንብ መሰረት ፕሮግራሞቻቸውን ማስተዋወቅ የሚችሉበት መድረክ የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በዋናነትም የፓርቲዎችን አጀንዳ ሀገርንና ሕዝብን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የሚኖረውን አንድምታ ለመራጩ ሕዝብ በቂ መረጃ ከመስጠት አንፃር የተሻሉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸውም ነው የጠቀሱት።