የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ደህንነትን ታሳቢ ያደረገ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ደህንነትን ታሳቢ ያደረገ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ደህንነትን ታሳቢ ያደረገ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በህግ የተሰጠውን የድንበር ቁጥጥር ለማከናወን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ድንበር ቁጥጥር ሥራ ያከናውናል፡፡
የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ዓለም አቀፍ ህግና አሰራርን ተከትለው በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፤ ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እንግዶችን ለመቀበል ያደረገውን ዝግጅትም አስጎብኝቷል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ በዚህ ወቅት፤ አገልግሎቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመዳረሻ ቪዛ፣ የገቢ መንገደኞች ልዩ አገልግሎት፣ የመውጫ ቪዛ እና የዓለም አቀፍ በረራ አስተናጋጆች አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ከዚህ ቀደም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሰጠው የመዳረሻ አገልግሎት የተንዛዛ፣ አሰልቺና ህግና አሰራርን ያልተከተለ እንደነበር አስታውሰው ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት በ11 የሪፎርም አጀንዳዎች በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ላይ ስር-ነቀል ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡
የመዳረሻ ቪዛ የሚጠይቁ የውጭ ሀገር ዜጎች ከሁለት ሰዓት በላይ ይጉላሉ እንደነበር አስታውሰው፤ በሪፎርሙ የቴክኖሎጂና የሰው ሀይል አቅምን በማሳደግ አገልግሎቱን በደቂቃ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ማንኛውም ዓለም አቀፍ ተጓዥ የሚገባውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ባለፉት 18 ወራት 240 በላይ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ወደ ሥራ ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ደህንነትን ታሳቢ ያደረገ ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ 39ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለማስተናገድ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶችን ማድረጓን በማስታወስ፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትም የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ይጠበቃል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማንኛውም ጊዜ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የሲ.ሲ.ቲቪ (CCTV) ካሜራ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሕብረቱን ጉባኤ የሚመጥን ዝግጅት ማድረጓን ገልጸው፤ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣንና ቀልጣፋ ሆኗል ብለዋል፡፡
በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመዳረሻ ቪዛ ክፍል ቡድን መሪ ገዛኽኝ ታደሰ፤ ከሪፎርሙ በፊት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ ኢትዮጵያን የማይመጥን የማንዋል አሰራር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሁሉም አገልግሎት በአንድ መስኮት እንዲጠናቀቅ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የሰለጠነ የሰው ሀይል አቅምን በማሳደግና የአገልግሎት መስጫ መስኮቶችን ከስድስት ወደ 21 በማሳደግ የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ድንበር አስተዳደር ቡድን መሪ ቶሎሳ ተገኜ በአየር መንገዱ የሚሰጠው የኢሚግሬሽን አገልግሎት በሰው ሀይልና በግብዓት የተሟላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከብቁ ባለሙያዎች ጋር አጣምረው እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው፤ የአገልግሎት መስጫ መስኮቶችም ወደ 28 አድገዋል ብለዋል፡፡
ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚገቡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት ስነ-ምግባርና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማስተናገድም በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡