የሻዕቢያ መንግስት የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል - የትግራይ ክልል ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሻዕቢያ መንግስት የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል - የትግራይ ክልል ነዋሪዎች
መቀሌ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦ የሻዕቢያ መንግስት የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር በሚገለጡ ድርጊቶች አሳይቷል ሲሉ በትግራይ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ጋር የተፈጠረው አለመግባባት መነሻው በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሽሬን ሲቆጣጠር የኤርትራ ጦር ተከትሎ በመግባት የግለሰቦችን ቤቶች እና ፎቆች ማፍረስ ሲጀምር መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
በአድዋ እና በአዲግራት ከተሞችም ፋብሪካዎችን በመዝረፍና ነቃቅሎ በመጫን እንዲሁም በአክሱም በወጣቶች ላይ የፈጸመው ግድያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከፍተኛ ጸብ ውስጥ ሊያስገባው ችሏልም ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በሽረ፣ በአክሱምና በመቀሌ ከተሞች የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ በሻዕቢያ የሚመራው የኤርትራ መንግስት የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር በሚገለጡ ድርጊቶች አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል።
የሽረ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ራህዋ አለማየሁ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የሻዕቢያ ወታደሮች ከሸራሮ ከተማ እስከ መቀሌ ዙሪያ በንፁሀን ላይ ግድያና ዘረፋን ጨምሮ አረመኔያዊ ተግባር መፈፀማቸውን አስታውሰዋል።
በተለይም በከተሞች ፋብሪካዎችንና የተለያዩ የህዝብ ሃብቶችን ነቃቅሎ በመጫን የሀገርና የህዝብን ሃብትና ንብረት በይፋ ዘርፈዋል ብለዋል።
በመሆኑም የሻዕቢያ መንግስት የኢትዮጵያን እድገት የማይሻ የህዝብ ጠላት በመሆን ከሰላም ይልቅ አለመረጋጋትን፤ ከእድገት ይልቅ ድህነትን የሚሻ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የአክሱም ከተማ ነዋሪ መምህር አብርሀም ተመስገን፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ከተሞች በሰዎችና በንብረት ላይ አስነዋሪ ተግባራትን መፈፀማቸውን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለምክር ቤት አባላት የሰጡት ማብራሪያም በተግባር ታይቶ ያለፈ እውነታ ነው ብለዋል።
በመቀሌ ዙሪያ እንደርታ ወረዳ በመሰቦ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መልአኩ በርኸ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ሰራዊት የቤት ንብረቶችን፣ ምርትና እንስሳትን ጭምር ዘርፈው ስለመውሰዳቸውም አስታውሰዋል።
በዚህም በርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸው ለመከላከል ጥረት ያደረጉት ላይም ያለርህራሄ ግድያ ስለመፈፀማቸው አንስተዋል።
በመሆኑም የኤርትራ መንግስት መቼም ቢሆን ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መልካም የማያስብ የጥፋትና የውድቀት ዓላማ ሰንቆ የሚሰራ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።