ቀጥታ፡

ዲጂታል የግብር አከፋፈል ስርዓት የግብር ከፋዮችን ጊዜና ገንዘብ ከብክነት ታድጓል 

አምቦ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-የአምቦ ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት የዘረጋው ዲጂታል የግብር መክፈያ ቴክኖሎጂ ሰርዓት በወቅቱ ግብራቸውን በመክፈል  ከጊዜና ከገንዘብ ብክነት የታደጋቸው መሆኑን የከተማው ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ግብር ከፋዮች አስተዳደሩ የዘረጋው ዲጂታል የግብር መክፈያ ስርአት ግብራቸውን በወቅቱና በተቀላጠፈ መንገድ ለመክፈል እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

የግብር አከፋፈል ሂደቱን አስመልክተው አስተያየታቸውን ከሰጡ በአምቦ ከተማ በሆቴል ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሙሉቀን ፍስሀ  እንዳሉት፤  ግብራቸውን  በወቅቱ በመክፈል ለከተማዋ እድገት የበኩላቸውን እየተወጡ ናቸው።


 

የከተማዋ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ግብራቸውን ከስራቸው ሳይነጠሉ  በቴክኖሎጂ  የሚከፍሉበትን አሰራር  መቀየሱ ከዚህ በፊት በመመላለስ ይጠፋ የነበረውን የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ብክነት እንዲሁም ብልሹ አሰራርን  ማስቀረቱን  ተናግረዋል ።

በጀበና ቡና ንግድ ላይ የተሰማራችው ወጣት ልዩ ጌታቸው በበኩሏ እንደገለጸችው፤ የገቢ ሰብሳቢ መስርያ ቤቱ  ቀልጣፋ አሰራር  በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉ አግዟል።


 

የመኖሪያ ቤት ግብራቸውን በቴሌ ብር  በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣታቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ አለሙ ጉቱ ናቸው፡፡


 

ግብር በወቅቱ መክፈል ለመንግስትም ሆነ ለማህበረሰብ  እድገት መሰረት ነው ያሉት አቶ አለሙ ዜጎች ግብራቸውን በታማኝነት በመክፈል ካላስፈላጊ ቅጣት ራሳቸውን ማዳን እንዳለባቸው መክረዋል።

የአምቦ ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጂፋራ ሂርጳ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ በስድስት ወራት  ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን  ብር በላይ የገቢ ግብር ተሰብስቧል፡፡


 

ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር  በላይ ብልጫ እንዳለው  ጠቅሰዋል።

ለከተማው የግብር ገቢ ማደግ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ሰራተኞች በቅንጅት መስራታቸውና ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግንዛቤ መሰጠቱ እንዲሁም  በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር መዘርጋቱን  ጠቅሰዋል፡፡

የገቢ አሰባሰቡን ለማሳለጥ ከተደረገው ተግባር ጎን ለጎን  የግብር ስወራን ለመከላከል በቅንጅት መሰራቱን  አመልክተዋል፡፡

 የከተማው ግብር ከፋዮች በወቅቱና በታማኝነት ግብራቸውን በመክፈል ላሳዩት ተነሳሽነት አመስግነው፤ያልከፈሉትም  ግብራቸውን  በወቅቱ እንዲከፍሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም