በመዲናዋ ለተኪ ምርት በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ለተኪ ምርት በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018(ኢዜአ)፦በመዲናዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራት የተኪ ምርቶች አቅርቦት በማደጉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ካካተቷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ግብ ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ይገኙበታል።
ከተማ አስተዳደሩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ባደረገው ተከታታይ ድጋፍና ክትትል፣ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት እንዲያድግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ለአብነትም 305 አነስተኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በሊዝ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ፣ ከዕቅዱ በላይ 340 ኢንዱስትሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የማምረት አቅም ከነበረበት 66 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 69 በመቶ ማደጉን አመልክተው በስድስት ወራት ውስጥ 238 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉንም ተናግረዋል።
በተኪ ምርት 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ምርት ማምረት ተችሏል ያሉት ከንቲባዋ ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ግብ ያሳካ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ገልጸው በሌላ በኩል 16 ሺህ 635 ቶን ምርት ወደ ውጭ በመላክ 123 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡