ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች በሀገራቸው ጉዳይ ተሳትፏቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ መድረክ  የፈጠረ ነው

አሶሳ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች በሀገራቸው ጉዳይ ተሳትፏቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ  መድረክ  የፈጠረ መሆኑን  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የአካል ጉዳተኞች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማህበረሰቡን በማወያየት የተሳታፊዎችና የአጀንዳ ልየታ ስራዎችን አከናውኗል።

ስራውንም በማስቀጠል  ሁሉንም አካላት በማሳተፍ የተሰበሰቡ  አጀንዳዎች ላይ በሳል ውይይት በማድረግ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት መሰረት  እንደሚጥል  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  መደበኛ ስብሰባ ላይ ማንሳታቸው ይታወሳል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪ የአካል ጉዳተኞችን  አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን  ቀዳም ባሉት ግዜያት ባካሄዳቸው አካታችና አሳታፊ ምክክሮች በንቃት መሳተፋቸውንም ገልጸዋል።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የአሶሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው እስከዳር ጥበቡ የምክክር ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞችና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በምክክሩ እንዲሳተፉ ማድረጉ አካታችነቱን ያረጋገጠ እንደሆነ ማሳያ ነው ብላለች።

ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው መድረክ ላይ ተሳታፊ እንደነበረች አስታውሳ በምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎችን በአግባቡ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም ገልፃለች።

ምክክሩ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ምቹ የመኖሪያ ካባቢ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግራለች።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ አዳነች አስራት በበኩላቸው፤ በክልል ደረጃ በተካሄደው የምክክር መድረክ ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ አካል ጉዳተኞች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።


 

የአካል ጉዳተኞች በምክክሩ መሳተፋቸው በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን የተሳሳተ ግንዛቤ የቀየረ እና አካል ጉዳተኞች ሃሳብ እንዳላቸው እና ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማድረጉን አብራርተዋል።

ምክክሩ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አስፈላጊነትን የሚያጠናክር እና ጦርነትን እንደ አማራጭ ለሚወስዱ አካላት ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም