ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የብራዚል ግንኙነት የደቡብ-ደቡብ ትብብር መርሆዎች ላይ የጸና ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ እና የብራዚል ግንኙነት የደቡብ-ደቡብ ትብብር መርሆዎች ላይ የጸና መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።

በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከል ያለውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የኢኮኖሚ ትብብር ፎረም በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ይህ ፎረም የሁለትዮሽ ግንኙነታችን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያመለክት ነው ብለዋል ።

ለንግድና ለኢኮኖሚ ትብብር የሚሆን ተስፋ ሰጪ የወደፊት አቅጣጫን በጋራ የምንቀርፅበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት አጋርነት የደቡብ-ደቡብ ትብብር መርሆዎች ላይ የጸና ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በብሪክስ እና በሌሎች የባለብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፎች ውስጥ ባለን የጋራ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እና የብራዚል የንግድ ልውውጥ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ እንደ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶች ያሉ እሴት የተጨመረባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ብራዚል መላክ መጀመሯ ለግንኙነቱ መጠናከር ማሳያ ነው ብለዋል።

በአንጻሩ ከብራዚል የግብርና ማሽነሪዎች እና የትራንስፖርት መሣሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ታስገባለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ የንግድ ልውውጥ መጀመሯን አስታውቀዋል።

ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም የብራዚል ባለሀብቶችም ኢትዮጵያን እንደ ስትራቴጂካዊ መግቢያ በመጠቀም ሰፊውን የአፍሪካ ገበያ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶስ ሳንቶ በበኩላቸው፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የብራዚል እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት አዲስ የትብብር ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

ለዚህም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኩል የተደረጉ ከፍተኛ የሥራ ጉብኝቶችን ጠቅሰው ይህም በመካከላችን ያለውን የጋራ መተማመን እና የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ያለንን የጋራ ራዕይ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) ፎረሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በፈረንጆቹ 2025 በሪዮ ዲ ጄኔሮ ባደረጉት ስብሰባ ላይ የተደረሰው ስምምነት ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

በፎረሙ የአፔክስ-ብራዚል (Apex-Brasil) እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲህም የብራዚል የግብርና እና እንስሳት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ስምምነት ፊርማ ተፈራረመዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም