ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል

ጂንካ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የዘርፉ ምሁራን ገለፁ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጂንካ ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሌንጮ ደሳለኝ እንዳሉት በዲጂታል ኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱን ለማዘመንና ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች እጅግ ውጤታማ ናቸው።


 

ከተቋማት ለአብነት የጂንካ ዩኒቨርስቲን የጠቀሱት ተመራማሪው በዩኒቨርስቲው ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የመማር ማስተማር ስራውን አንድ እርከን ማሳደጉን ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርስቲው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህም ጥራቱን የጠበቀና በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት አስችሏል ብለዋል።

የፈተና አሰጣጡም በበይነ መረብ አማካኝነት መሆኑም ኩረጃና የፈተና ስርቆትን ለመከላከል እንዳስቻለ ጠቁመው የተማሪዎች የውጤት አያያዝም ከስህተት በፀዳ መልኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን አስችሏል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂው በተለይ የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ ትልቅ ሚናን እየተጫወተ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በዩኒቨርስቲው የኤሌክትሮንክስ የትምህርት ክፍል ዳይሬክተር እና የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ መምህርና ተመራማሪ እሸቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ኢንሼቲቭ ዘመናዊ የንግድና የገንዘብ ልውውጥ እንዲስፋፋ አድርጓል።


 

በቴሌ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግ እና በሌሎችም ፈጣን የዲጂታል የገንዘብ ልውውጦች እንዲኖሩ በማድረግ የንግድ ስርዓቱ እንዲዘምን አድርጓል ብለዋል።

በተለይ የዲጂታል መታወቂያው ወንጀልን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዜጎች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተጣጣመ ማህበረሰብን ለመፍጠር የተጀመረው ስራና በተለይ በኢትዮ ኮደርስ የወጣቱን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ጠቁመው ሀገራችን ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የምትሆንበትን መደላድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል።

በተለይ በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርስቲ ለማቋቋም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው ንቅናቄ በሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ልህቀት እንዲመጣ ያስችላል ብለዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በምርምር፣ በህክምና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በመከላከያ እና በሌሎች የስራ መስኮች የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም