ቀጥታ፡

የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነታችንን አሳድጎልናል- አርሶ አደሮች

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የተፋሰስ ልማት ስራው የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደጉን በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እየተካሔደ ያለው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የመሬት ለምነትን በመመለስ ምርታማነት ለማሳደግ እያስቻለ ነው።


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ኦፋ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ሜጊሶ እና ማርታ አዋሾ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መጀመሩ በጎርፍ እየተጠረገ ይወሰድ የነበረውን ለም አፈር ጥቅም ለይ ለማዋል አስችሎናል  ይላሉ።


 

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ሳቢያ  የደረቁ ምንጮች ዳግም እንዲፈልቁ በማድረጉ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲለሙ ማድረጉን አመልክተዋል።


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አበራሽ አቡቶ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሰራው  የተራቆጡ አካባቢዎች ዳግም እንዲለሙ ማድረጉን ተናግረዋል ።

በዚህም የተለያዩ የጓሮ አትክልት በማምረት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቅሰው የተፋሰስ ልማት ስራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያመለከቱት ።


 

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው፤ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው ምርታማነት በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው።

ባለፉት ዓመታት በተሰራው ስራ እንደ ሀገር አደጋ ላይ ከነበሩ 54 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ዳግም እንዲያገግም ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።።

በተለይም የአፈር ለምነትን በመጨመር፣ የደረቁ ምንጮች ዳግም እንዲፈልቁ በማድረግ እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጉልህ ሚና መጫወቱንም ነው ያነሱት።


 

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው ዓመትም 25 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ23 ሺህ ተፋሰሶች ላይ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ እየታየ ያለው የህብረተሰብ የተሳትፎ ባህል መጠናከር እንደሚገባውም አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም